ማክሰኞ 30 ኦገስት 2016

እውነት

እውነት
እውነት ፤ ምንድነው  ?

እውነት የነፍስ ትክክለኛ ምስጢር ናት ፤የነፍስም ትክክለኛነት ያለው በእውነት ውስጥ ነው ። እውነት የሌላት ህይወት በጨለማ ውስጥ የታሰረች ናት ፤አለም ውበትን ያገኘችው ህያውነት ባላት ነፍስ ሲሆን ፤ነፍስ  ደግሞ  ለመላእክት ፤ለሰው ፤ ለእንስሳ  ከአምላክ ዘንድ  የተበረከተች ውብ በረከትና ስጦታ ናት ።  የመልአክ ነፍስ አንዴ ከአምላክ ይሰጠዋል ለዘለአለም ከእርሱ ጋር ይኖራል በሞት አይወሰድበትም ፤ አይሞትምና ። የሰው ነፍስ አንዴ ከአምላክ ይሰጠዋል እንደገና በሞት ይወሰድበታል በትንሣኤ እንደገና ይሰጠዋል/ይመለስለታል/ ። የእንስሳ ነፍስ ከአምላክ አንዴ ይሰጠዋል እንደገና በሞት ይወሰድበታል ፤ለዘለአለም አይመለስለትም ፤ትንሣኤ የለውምና ። ስለዚህ እውነት በሞት በማይወሰድባቸው መላእክትና እንደገና ከሞት በኋላ በትንሣኤ ለዘለአለም የመኖር ፀጋ በተሰጠው የሰው ዘር ነፍስ ውስጥ የምትፈለግ ቀዳሚ ጉዳይ ናት ። መላእክትንም ሆነ ሰዎችን በአምላክ ፊት የሚያስከብራቸውና ቦታ የሚያሰጣቸው  በተፈጠሩ ሰዓት የተሰጠቻቸው እውነት ቦታዋን ጠብቃ ሥትገኝ ብቻ ነው ።

እግዚአብሔር ከእውነትና ከእውነተኞች ጋር ብቻ የሚስማማ ንጹህ አምላክ ነው። እግዚአብሔር የእውነት ዳኛ ነው  እንዲል መጽሐፍ ፤መዝ 7 ፤11   እውነትን የሚገፋ ሁሉ በእርሱ ዘንድ የተጠላና የተናቀ ነው ፤ ስለዚህ ውሽትን አስወግዳችሁ ፤እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ ። ወደ ኤፌሶን  4፤25  ማንም ቢሆን የተሰጠውን ተስፋና ፤የሕይወት ምድር  መውረስ የሚችለው በእውነት የተቀመመ ማንነት ሲኖረው ብቻ ነው። በዚህ መንገድ ያልተገኙትን ፤አለቅነታቸውን የረሱትን ከእውነት ጋር የተጣሉትን የሰማይ መላእክትን እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር እንዲወድቁ ፈርዶባቸዋል ። « መኖሪያቸውንም የተውትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን ፤መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ  ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል » ። ይሁዳ 1 ፤6 ።

« ለመላእክትሂ ፤ኢትክህሎሙ ድንጋሌ ሕሊና ፤እስመ አበሱ በፍትወት ፤ወወረዱ ምድረ በመዋእል ዘቀዳሚ » ። ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ለመላእክት እንኳን አልተቻላቸውም በቀደመው ወራት ያልተሰጣቸውን ሽተው በድለው ከሰማይ ወደ ምድር ወርደዋልና ። / ተአምረ ማርያም መቅድም /

እውነትን አለማስበ፤ ጽድቅንም አለማድረግ ፤ እንደሚጠበቅብንም አለመገኘት ከክብር መውረድ ብቻ ሳይሆን ከሰውነት   ወደ እንስሳነት መለወጥ ነው  ። ከእውነት ጋር የማይተባበር ሁሉ ተፈጥሮውን ያዛባዋል ። ብዙ ጨካኝና ከአውሬ ይልቅ በሰው ላይ የከፉ ሰዎች መነሻቸው በውስጣቸው የነበረው እውነት መሞት ነው ።ስለእውነት  የሚያስብና ለእውነትም የሚታዘዝ ልብ የላቸውምና በሔዱበት ሁሉ አደጋና ሥጋት ናቸው ። እንደ ሰው ሳይሆን እንደ አውሬ ይፈራሉ ።ሰው ተውዶ ሲፈራ ክብር ነው ። ከሚያመጣው ክፉ ነገር የተነሳ የሚፈራ ከሆነ ለፈሪው፤ ተፈሪው አውሬ ነው ። እለት፤ እለት ልባቸው እውነትን የማፈለቅ ኃይል  የነበረው  እንደ አብርሐም ያሉ ደጋጎች በእግዚአብሔር ቃል ለበረከት ሁኑ ተብለዋል ።ዘፍ 12 ፤2 አስፈሪነታቸው ከእምነታቸውና ፤ ከእግዚአብሔር ቃል የተነሳ ነውና ።    






እውነት ከጌጥ በላይ ከወርቅ ፤ከእንቍ በላይ ታምራለች ። እግዚአብሔርን የሚያውቁ ብቻ ያጌጡባታል ። ወርቅ በጨለማ ወርቅነቱ አይታወቅም ቢታይ እንኳ በቀን እንዳዩት አይሆንምና ውበቱ የጎላ አይደለም ። እውነትም ጨለምተኛ አስተሳሰብ ላላቸው ሰዎች ሁሉ የማታምር ውበት ያጣች ናት ። የሥጋም ሆነ የልብ አይን በብርሐን ደስ ይለዋል በእርሷ ሁሉን ያያልና ። ብርሐን ከሌለ አይን ምንም ነው፡፡ እውነት ከሌለም የሰውም ህይወት ከንቱና ከጨለማ የባሰ ድቅድቅ ጨለማ ነው ። እውነት የሌለው ሁሉ በጨለማ ይኖራል ።

እውነት የሌለው ሞራልና ፤መንፈሳዊ ድፍረት የለውም ፤መንገዱ ሁሉ በፍርሐት፤በሽብር የተመላ ነው ። ለእውነተኛ ሰው ግን ምንም  በማይታይበትና ድቅድቅ በሆነበት ስፍራ ሁሉ ለእርሱ ብርሐን አለው ። ምክንያቱም የእርሱ ብርሐን ከውጭ የተቀጠለ ሳይሆን ከሆዱ የሚፈልቅ ነው ። የሆነው ነገር የማያስፈራ ሆኖ ሳይሆን ስለማይፈራ ነው ። ለዚህም ነው ዳዊት « ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ ፤ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም » ያለው መዝ ዳዊት 46 ፤2






አባቶቻችን እሳትን ለመርገጥ ፤ከአንበሳ ጥርስ ለማምለጥ ፤ አቅመኞች የሆኑት በውስጣቸው እውነት ስለነበር ነው ።እውነት ቀና ብሎ ለመራመድ ብቃት ፤ ልፍስፍስና ሞራል የለሽ በሆነ አለም ውስጥ እንደ አንበሳ ደቦል ያለ ሥጋት ማስኬድ የሚችል መተማመኛ ነው ።

እውነትን ለማግኘት የሚደረግ ትግል ፤ ወርቅን ከመሬት ለማግኘት ከሚደረግ ቍፋሮ ይልቅ እጅግ ከባድ ነው ። የተገኘች ቀን ግን ተቆፍሮ እንደተገኘው ወርቅ ዋጋዋ በገንዘብ አይተመንም ። እውነት በዚህ ዋጋ ትሸጣለች አትባልም ። ወርቅ በእሳት ይቀልጣል ፤እውነት ግን ትሽፈናለች እንጂ አትጠፋም ። እውነትን ለዘለአለም መግደል የሚችል ኃይለኛ አልታየም ፤ የለምም ። የሮማው ገዚ እውነት ምንድነው? ብሎ ጠየቀ ዮሐ 18 ፤38  

ወንድሜ እውነት ለአንተ ምንድነው ?  

በእናቱ አቡኑ የተባለው ካህን ጻፈው  ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ