ማክሰኞ 30 ኦገስት 2016

ABRAHA WE-ATSBAHA

Ethiopia shall soon stretch out her hands unto God.

ABRAHA WE-ATSBAHA 
ግማሽ አካሉን ከምድር ውስጥ የሸሸገ አስገራሚ መስህብ ነው፡፡ ከአለት ተጠርቦ የተሰራው እና ከተፈለፈለበት አብይ አለት ጋር ሳይላቀቅ የቆመው ቅርስ ያፈዛል፡፡ ያላየው አይፈዝምና እንዴት አትበሉኝ፤ ከዐለቱ የመስቀል ቅርጽ ያለው ህንጻ ቤተ ክርስቲያን፤ ስፋቱ 16 ሜትር በ13 ሜትር ነው፡፡
የጣሪያው ቁመት ሰባት ሜትር ይደርሳል፡፡ 13 የሚሆኑት ጣሪያውን ደግፈው የቆሙት አምዶች ግዙፍና ድንቅ ናቸው፡፡ በሐረግ ሥነ-ጥበብ ያጌጠው ጣሪያ ቀና ብሎ ለሚመለከተው ሰው አድናቆትን ያጭራል፡፡
ቄሰ ገበዙ መጡ፤ ሰላምታ ተለዋወጥን፤ አማርኛ እየቸገራቸው ጉዳዬን ነገርኳቸው፡፡ ከፈቱልኝ፡፡ አብረውኝ ያሉትን ይበልጥ በማመን እንደከፈቱልኝ ገብቶኛል፡፡
ውስጡ ደግሞ ልዩ ነው፡፡ ሶስት አብያተ መቅደሶች አሉት፤ ቀኙ የቅዱስ ሚካኤል ግራው የቅዱስ ገብርኤልና መካከሉ ደግሞ የቅድስት ማርያም ታቦተ መንበሮች አሉበት፡፡ አስደናቂው ውቅር ውስጣዊ ውበቱ ከተሰራበት ዘመን ጋር ሲነጻጸር ተአምር ነው፡፡ በአንዳንድ የውጪ ጸሐፍት ዘንድ በትግራይ ካሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚበልጥ እንደሆነ ተገምቷል፡፡
በውቅሩ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሳሉት መንፈሳዊ ስዕሎች በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተሰሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጥንታዊና እና እጹብ የሥነ ሥእል ውጤቶች መካከል የአባ ሰላማ ፍሬምናጦስ ስእል ይገኝበታል፡፡ በተመሳሳይ በቅኔ ማህሌቱ የሚታዩት ስእሎችም የጻድቃን፣ የመላእክትና የሰማእታትን ገድሎች ያሳያሉ፡፡
አንዳንዶች የተሰራበት ዘመን ላይ የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም፤ የደብሩ አስጎብኚ ግን በ4ኛው ክፍለ ዘመን የተሰራ እንደሆነ ከእርግጠኝነት አልፈው ነገሩኝ፡፡ የሳቸውን ማመን ይሻላል፡፡
ስላየሁት ልንገራችሁ የአባ ሰላማ መስቀል፣ ደግሞ የአብረሃ ወ አጽበሃ የወርቅ ጫማን፣ ወንበራቸውን…..እንዴት የታደለ ስፍራ ነው፡፡

እውነት

እውነት
እውነት ፤ ምንድነው  ?

እውነት የነፍስ ትክክለኛ ምስጢር ናት ፤የነፍስም ትክክለኛነት ያለው በእውነት ውስጥ ነው ። እውነት የሌላት ህይወት በጨለማ ውስጥ የታሰረች ናት ፤አለም ውበትን ያገኘችው ህያውነት ባላት ነፍስ ሲሆን ፤ነፍስ  ደግሞ  ለመላእክት ፤ለሰው ፤ ለእንስሳ  ከአምላክ ዘንድ  የተበረከተች ውብ በረከትና ስጦታ ናት ።  የመልአክ ነፍስ አንዴ ከአምላክ ይሰጠዋል ለዘለአለም ከእርሱ ጋር ይኖራል በሞት አይወሰድበትም ፤ አይሞትምና ። የሰው ነፍስ አንዴ ከአምላክ ይሰጠዋል እንደገና በሞት ይወሰድበታል በትንሣኤ እንደገና ይሰጠዋል/ይመለስለታል/ ። የእንስሳ ነፍስ ከአምላክ አንዴ ይሰጠዋል እንደገና በሞት ይወሰድበታል ፤ለዘለአለም አይመለስለትም ፤ትንሣኤ የለውምና ። ስለዚህ እውነት በሞት በማይወሰድባቸው መላእክትና እንደገና ከሞት በኋላ በትንሣኤ ለዘለአለም የመኖር ፀጋ በተሰጠው የሰው ዘር ነፍስ ውስጥ የምትፈለግ ቀዳሚ ጉዳይ ናት ። መላእክትንም ሆነ ሰዎችን በአምላክ ፊት የሚያስከብራቸውና ቦታ የሚያሰጣቸው  በተፈጠሩ ሰዓት የተሰጠቻቸው እውነት ቦታዋን ጠብቃ ሥትገኝ ብቻ ነው ።

እግዚአብሔር ከእውነትና ከእውነተኞች ጋር ብቻ የሚስማማ ንጹህ አምላክ ነው። እግዚአብሔር የእውነት ዳኛ ነው  እንዲል መጽሐፍ ፤መዝ 7 ፤11   እውነትን የሚገፋ ሁሉ በእርሱ ዘንድ የተጠላና የተናቀ ነው ፤ ስለዚህ ውሽትን አስወግዳችሁ ፤እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ ። ወደ ኤፌሶን  4፤25  ማንም ቢሆን የተሰጠውን ተስፋና ፤የሕይወት ምድር  መውረስ የሚችለው በእውነት የተቀመመ ማንነት ሲኖረው ብቻ ነው። በዚህ መንገድ ያልተገኙትን ፤አለቅነታቸውን የረሱትን ከእውነት ጋር የተጣሉትን የሰማይ መላእክትን እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር እንዲወድቁ ፈርዶባቸዋል ። « መኖሪያቸውንም የተውትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን ፤መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ  ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል » ። ይሁዳ 1 ፤6 ።

« ለመላእክትሂ ፤ኢትክህሎሙ ድንጋሌ ሕሊና ፤እስመ አበሱ በፍትወት ፤ወወረዱ ምድረ በመዋእል ዘቀዳሚ » ። ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ለመላእክት እንኳን አልተቻላቸውም በቀደመው ወራት ያልተሰጣቸውን ሽተው በድለው ከሰማይ ወደ ምድር ወርደዋልና ። / ተአምረ ማርያም መቅድም /

እውነትን አለማስበ፤ ጽድቅንም አለማድረግ ፤ እንደሚጠበቅብንም አለመገኘት ከክብር መውረድ ብቻ ሳይሆን ከሰውነት   ወደ እንስሳነት መለወጥ ነው  ። ከእውነት ጋር የማይተባበር ሁሉ ተፈጥሮውን ያዛባዋል ። ብዙ ጨካኝና ከአውሬ ይልቅ በሰው ላይ የከፉ ሰዎች መነሻቸው በውስጣቸው የነበረው እውነት መሞት ነው ።ስለእውነት  የሚያስብና ለእውነትም የሚታዘዝ ልብ የላቸውምና በሔዱበት ሁሉ አደጋና ሥጋት ናቸው ። እንደ ሰው ሳይሆን እንደ አውሬ ይፈራሉ ።ሰው ተውዶ ሲፈራ ክብር ነው ። ከሚያመጣው ክፉ ነገር የተነሳ የሚፈራ ከሆነ ለፈሪው፤ ተፈሪው አውሬ ነው ። እለት፤ እለት ልባቸው እውነትን የማፈለቅ ኃይል  የነበረው  እንደ አብርሐም ያሉ ደጋጎች በእግዚአብሔር ቃል ለበረከት ሁኑ ተብለዋል ።ዘፍ 12 ፤2 አስፈሪነታቸው ከእምነታቸውና ፤ ከእግዚአብሔር ቃል የተነሳ ነውና ።    






እውነት ከጌጥ በላይ ከወርቅ ፤ከእንቍ በላይ ታምራለች ። እግዚአብሔርን የሚያውቁ ብቻ ያጌጡባታል ። ወርቅ በጨለማ ወርቅነቱ አይታወቅም ቢታይ እንኳ በቀን እንዳዩት አይሆንምና ውበቱ የጎላ አይደለም ። እውነትም ጨለምተኛ አስተሳሰብ ላላቸው ሰዎች ሁሉ የማታምር ውበት ያጣች ናት ። የሥጋም ሆነ የልብ አይን በብርሐን ደስ ይለዋል በእርሷ ሁሉን ያያልና ። ብርሐን ከሌለ አይን ምንም ነው፡፡ እውነት ከሌለም የሰውም ህይወት ከንቱና ከጨለማ የባሰ ድቅድቅ ጨለማ ነው ። እውነት የሌለው ሁሉ በጨለማ ይኖራል ።

እውነት የሌለው ሞራልና ፤መንፈሳዊ ድፍረት የለውም ፤መንገዱ ሁሉ በፍርሐት፤በሽብር የተመላ ነው ። ለእውነተኛ ሰው ግን ምንም  በማይታይበትና ድቅድቅ በሆነበት ስፍራ ሁሉ ለእርሱ ብርሐን አለው ። ምክንያቱም የእርሱ ብርሐን ከውጭ የተቀጠለ ሳይሆን ከሆዱ የሚፈልቅ ነው ። የሆነው ነገር የማያስፈራ ሆኖ ሳይሆን ስለማይፈራ ነው ። ለዚህም ነው ዳዊት « ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ ፤ተራሮችም ወደ ባህር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም » ያለው መዝ ዳዊት 46 ፤2






አባቶቻችን እሳትን ለመርገጥ ፤ከአንበሳ ጥርስ ለማምለጥ ፤ አቅመኞች የሆኑት በውስጣቸው እውነት ስለነበር ነው ።እውነት ቀና ብሎ ለመራመድ ብቃት ፤ ልፍስፍስና ሞራል የለሽ በሆነ አለም ውስጥ እንደ አንበሳ ደቦል ያለ ሥጋት ማስኬድ የሚችል መተማመኛ ነው ።

እውነትን ለማግኘት የሚደረግ ትግል ፤ ወርቅን ከመሬት ለማግኘት ከሚደረግ ቍፋሮ ይልቅ እጅግ ከባድ ነው ። የተገኘች ቀን ግን ተቆፍሮ እንደተገኘው ወርቅ ዋጋዋ በገንዘብ አይተመንም ። እውነት በዚህ ዋጋ ትሸጣለች አትባልም ። ወርቅ በእሳት ይቀልጣል ፤እውነት ግን ትሽፈናለች እንጂ አትጠፋም ። እውነትን ለዘለአለም መግደል የሚችል ኃይለኛ አልታየም ፤ የለምም ። የሮማው ገዚ እውነት ምንድነው? ብሎ ጠየቀ ዮሐ 18 ፤38  

ወንድሜ እውነት ለአንተ ምንድነው ?  

በእናቱ አቡኑ የተባለው ካህን ጻፈው  ።

ረቡዕ 20 ጁላይ 2016

ሊቀ መላኢክቱ ቅዱስ ሚካኤል

"እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ" (ዳን 10፡21).

ለመሆኑ ወጣትነት ምን ማለት ይሆን?

ወጣትነት ማለት ከለጋነት፣ከህፃንነትና ካለአዋቂነት እየወጣ፣ እየተላቀቀ ያለ ገና ብዙ የሚያድግ፣ የሚበረታ፣ የሚሰራ፣የሕፃንነትንም ሆነ የሽምግልና ችግሮች ተጽዕኖ የሚታይበት ብርቱነት፣ ኃያልነት ማለት ነው፡፡
ነገር ግን ኃይል ያለቁጥጥር አውዳሚ አጥፊ ሌላውን ብቻ ሳይሆን ራሱ ኃይል የሚመነጭበት አካል የሚያወድም ይሆናል፡፡ ወጣትነትም
የሚገታው፣ የሚገድበው ነገር ካልተበጀለት እንዲሁ ስለሚሆን ሰው ይህ ችግር እንዳይገጥመው “ፈጣሪህን አስብ” በሚለው ሐረግ ለራሱ ገደብና ልጓምን አበጅቶ ይህንን ኃይል(የወጣትነት ጸጋ) በአግባቡ እንዲጠቀምበት ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፡፡
በዚህም አንፃር ወጣትነትን በሚገባ ይዘው ከተጠቀሙበት ብዙ ፀጋዎች እንዳሉት ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ያስተምረናል “ …ጎበዞች ሆይ ብርቱዎች ስለሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር
ክፉውንም ስለአሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ፡፡” 1ኛዮሐ2፡14፡፡ እንግዲህ ይህ ኃይለ ቃል የሚያሳየን ወጣትነት የብርታት ዘመን፣የኃይል ዘመን ማለት ትልልቅና አስደናቂ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ የሚሰራበት መሆኑን፣ የማስተዋል፣ ዕውቀትን/ምስጢርን/ በልብ ይዞ ውጤታማ ፍሬያማ የሚኮንበት የጸጋ ዘመን መሆኑን ያሳያል፡፡ ከሱ ጋር ተያይዞ ከባድ
ፈተና የሚስተናገድበት የሕይወት ምዕራፍ ስለሆነም የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን ምክር እንድንይዝ ግድ ይለናል፣ለመንፈስ ልጁ ለጎልማሳው /ለወጣቱ/ ለጢሞቲዎስ ሲመክረው “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ”
ብሎታል፡፡2ኛ ጢሞ2፡22 ወጣቶችም ይህንን ምክር ተግባራዊ ቢያደርጉ መልካም እንደሚሆንላቸው ሲያሳይ … ክፋውንም ስላሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ ብሏል፡፡
በዚህም የወጣትነት የሕይወት ምዕራፍ የእግዚአብሔርን ጸጋ ተቀብለው
የተጠቀሙበትና ክብር የተጎናጸፉ ብዙዎች ቅዱሳንን ማየት ይቻላል፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ስማቸው ተጠቅሶ ከምናገኛቸው ቅዱሳን አብዛኛዎቹ በወጣትነት ሕይወታቸው እግዚያብሔርን ደስ ያሰኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ያህልም፡-
ዮሴፍ ከፈተና አምልጦ ያንን ሁሉ ክብር ያገኘው፤ ለወገኖቹ ከጥፋት የመዳን ምክንያት የሆነው በወጣትነት የተሰጠውን ጸጋ በአግባቡ
ስለተጠቀመበት ነው፡፡/ዘፍ41፣40-57/
በባቢሎን ሀገር ይኖሩ የነበሩት ሦስቱ ወጣቶች /ሠለስቱ ደቂቅ/ እና ነቢዩ ዳንኤል በዚያ ሀገር ከሚገኙ አዋቂዎች ሁሉ በጥበብ ልቀው የነተኙት፤ ፈተና ቢፈራረቅባቸውም በመንፈሳዊ ልዕልና ፈተናውን ድል አድርገው በባቢሎን ሀገር ሁሉ የተሸሙት የወጣትነት ጸጋቸውን በአግባቡ
ስለተጠቀሙበት ነው፡፡ ዳን. 1-6÷20፣ ዳን.13÷30፣ ዳን. 61÷18/
ከላይ ለአብነት ከተጠቀሱት ባሻገር እነ ንጉስ ዳዊት ጠቢቡ ሰለሞን እነ ኤርሚያስ ነቢይ እነ ሶምሶን ሌሎችም ታሪካቸውን ለመናገር ጊዜ
የሚያጥረን ውዱሳን በዚህ እድሜ ተጠርተው በተሠጣቸው ፀጋ በአግባቡ በመጠቀማቸው ክፉውን ድል ነስተው እግዚአብሔር ደስ
የሚሠኝበትን ለመማበርከት በቅተዋል፡፡ ይህ ለመሆኑ መሠረታዊ ምክንያቱ ከእግዚአብሔር ጋር ሲኖሩ እንደ እግዚአአብሔር ቃል ስለተመላለሱ እንደሆነ ቅዱስ ዳዊት “ጎልማሳ መንገዱን በምን ያቀናል ቃልህን በመጠበቅ ነው” በማለት አረጋግጧል /መዝ 118፤9/
ከእግዚአብሔር ጋር ካልኖርንና እንደ እግዚአብሔር ቃል ካልተመላለስን በወጣትነት የሚገኝ ጸጋ ያለ ጥቅም ይባክናል፡፡ ትርፍ የሌለው መክሊት፣
ዱቄቱን ያላቦካ እርሾ፣ ጠፍቶ ያልተገኘ ድሪም፣ በውጭ የቀረውን ልጅ ይሆናል በዚህ ብቻ አያበቃም ወጣትነትም እምቅ ኃይል ስለሆነ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ካልተቆጣጠርነው ይህ ኃይል ለሌላው ጥፋት ሁሉ ምክንያት ከሆነ በኋላ ራሱ ያጠፋል፡፡ አዲስ መስመር የወጣትነት ፀጋ ማለት ምናብ አይደለም፡፡ ያለውን መልካም ሀብት ጠብቆ ለቤተ ክርስቲያን ለሀገር ለዓለም ሁሉ አዲስ ግኝት (Breakthrough) የሚያመጣ የሰላም አእምሮ ማለት ነው /መዝ 118-97-100/፣ ጠላትን
አስወግዶ ለህዝብ ልጆች ነጻነትን የሚያጎናጽፍ ብርቱ ሥራዎችን አከናውኖ የወገን ችግርን የሚቀርን የሚቀርፍ ጉልበት ነው /1ኛ ሳሙ
17፤41-49፣ መሳ 16፤30-31/፣ አዲስ የወይን ጠጅ የሞላበት አዲስ ረዋት /አቁማዳ/ ነው፡፡ አዲሱን የማይለወጠውን የእግዚአብሔር ሥራ
መሥራት የሚያስችለን ጸጋ ማለት ነው /ሉቃ 5፤38/፡፡ ወይኑን የሚያፈላው፣ ፍላቱን የሚችለው ጣዕም የሚያስገኝ መገልገያ ነው፡፡
የወጣትን ጸጋ ማለት! በዚህ ጸጋ የተጠቀምን ምን ያህል? በአግባቡ ባለመጠቀማችን
የተጎዳንስ? ራሳችንን በዙሪያችን ያሉትን እንመዝን ባለማስተዋል ያባከነውን መክሊት እናትርፍበት፣ የጠፉብንን ይህንን የልጅነት ድሪም አጥብቀን እንፈልገው በእግዚአብሄር ቃል እርሾነት ያልቦካውን /ያልተለወጠውን/ ትውልድ እንለውጥበት፣ የጠፋውን ልጅነትና ማንነት
ወደ አባቱ እንመልስበት እንዲ ሲሆን ወጣትነት አቤት ሲያምርበት!!! /ሉቃ
15፤3-24/ —

እግዚአብሔር፡እረኛዬ፡ነው፥ The Lord is my shepherd

እግዚአብሔር፡እረኛዬ፡ነው፥
መዝሙር፡22፡(23)።
የዳዊት፡መዝሙር።
1፤እግዚአብሔር፡እረኛዬ፡ነው፥የሚያሳጣኝም፡የለም።
2፤በለመለመ፡መስክ፡ያሳድረኛል፤በዕረፍት፡ውሃ፡ዘንድ፡ይመራኛል።
3፤ነፍሴን፡መለሳት፥ስለ፡ስሙም፡በጽድቅ፡መንገድ፡መራኝ።
4፤በሞት፡ጥላ፡መካከል፡እንኳ፡ብኼድ፡አንተ፡ከእኔ፡ጋራ፡ነኽና፥ክፉን፡አልፈራም፤በትርኽና፡ምርኵዝኽ፡እነር ሱ፡ያጸናኑኛል።
5፤በፊቴ፡ገበታን፡አዘጋጀኽልኝ፡በጠላቶቼ፡ፊት፡ለፊት፡ራሴን፡በዘይት፡ቀባኽ፥ጽዋዬም፡የተረፈ፡ነው።
6፤ቸርነትኽና፡ምሕረትኽ፡በሕይወቴ፡ዘመን፡ዅሉ፡ይከተሉኛል፥በእግዚአብሔርም፡ቤት፡ለዘለዓለም፡እኖራለኹ።
The Lord is my shepherd; I shall not want. He maketh me to lie down in green pastures: he leadeth me beside the still waters. He restoreth my soul: he leadeth me in the paths of righteousness for his name's sake. Yea, though I walk through the valley of the shadow of death, I will fear no evil: for thou art with me; thy rod and thy staff they comfort me. Thou preparest a table before me in the presence of mine enemies: thou anointest my head with oil; my cup runneth over. Surely goodness and mercy shall follow me all the days of my life: and I will dwell in the house of the Lord for ever.

አሥርቱ ትዕዛዛት

ከእግዚአብሔር አምላክ በቀጥታ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የተሰጠ ሕግ ነው፡፡ የተሰጡትም እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ በ3ኛው ወር ፋሲካን ካከበሩ በ3ኛው ቀን በደብረ ሲና ሰፍረው ሳለ ነበር፡፡ ዘፀ. 19፡1-4 በዘዳ. 34፡28 ዘዳ. 4፡13 ላይ አሥሩ ትዕዛዛት አሥር መሆናቸውን እንረዳለን፡፡
በዝርዝር ተጽፈው የሚገኙት ግን በዘዳ. 20፡ 3 እና17 እና ዘዳ. 5፡5-21 ላይ ነው፡፡ አሥርቱ ቃላትና ስድስቱ ቃላተ ወንጌል ለእስራኤል ዘስጋና ለእስራኤል ዘነፍስ የተዘጋጁ ስለሆነ ሁላችንንም ይመለከታል፡፡ እነርሱም፡-
1. ‹‹ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ›› ዘፀ. 20፡2-6
2. ‹‹ የእግዚአብሔር የአምላክን ስም በከንቱ አትጥራ፡፡ ›› ዘፀ. 20፡7
3. ‹‹ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ /አክብረውም/ ›› ዘፀ. 20፡ 8
4. ‹‹ አባትህንና እናትህን አክብር ›› ዘዳ. 20፡12
5. ‹‹ አትግደል ›› ዘፀ. 20፡13
6. ‹‹ አታመንዝር ›› ዘፀ. 20፡14
7. ‹‹ አትስረቅ ›› ዘፀ. 20፡15
8. ‹‹ በሐሰት አትመስክር ›› ዘፀ. 20፡16
9. ‹‹ አትመኝ ›› ዘፀ. 20፡17
10. ‹‹ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ ›› ዘሌ. 19፡18
- አሥርቱ ሕግጋት የብሉይ ኪዳን መሠረቶች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግ ብትጠብቁ ብትፈጽሙትም ሕዝቤ ትሆናላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ ብሎ ቃልኪዳን ገባ፡፡ ሕዝቡም በአንድ አፍ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ‹‹እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለን›› ብለው ቃል ኪዳን ገቡ፡፡ ዘፀ. 19፡8፤ 24፡1-8 ቅዱስ ጳውሎስም እንደነገረን ይህ ፊተኛው ኪዳን ያለ ደም አልተመረቀምና ዕብ. 18፡ 22 ሙሴ ኪዳኑን ለማጽናት የደም መርጨትን ሥርዓት እንዳደረገ በሐዲስ ኪዳንም ቢሆን ሥነ ሥርዐቱ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያላቸው ሕግጋት ናቸው፡፡ ማቴ 5፡17፣ 19፡15-22 ፣ዮሐ1፡12 እግዚአብሔር ሕዝቦቹና ልጆቹ ሊያረገን ይህን ታላቅ ተስፋ በመስጠት ቃል ከገባልን እኛ ደግሞ ትዕዛዙን ለመጠበቅ ምን ያህል ቃል ገብተንለታል? ጌታችን ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ ዮሐ 14፡15 እንዲሁም ከሆነ እንደ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለን ብለን ከሁሉ በፊት ለእግዚአብሔር ቃል መግባት አለብን፡፡ ክርስትናውን ስንጀምር የመጀመርያ ሥራችን መሆን ያለበት ይህ ነው፡፡
የዐሥርቱ ትዕዛዛት አከፋፈል
የክርስቲያን ሕግ የፍቅር ሕግ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞበታል ካለ በኋላ ከዐሥርቱ ትዕዛዛት የተወሰኑትን በመጥቀስ ፍቅር የሕግ ሁሉ ፍጻሜ መሆኑን በግልጽ ይነግራል፡፡ ሮሜ 13፡8-10 ታዲያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረ ፍቅር በሁለት ይከፈላል፡፡ ማቴ 22፡34-41
1 ፍቅረ እግዚአብሔር 
2 ፍቅረ ቢጽ
1. ፍቅረ እግዚአብሔር ከአንደኛ ትዕዛዝ እስከ ሦስተኛው ያሉት ሲሆኑ እግዚአብሔርን የሚመለከቱ ናቸው፡፡
2. ፍቅረ ቢጽ ከአራተኛ ትዕዛዝ እስከ አሥረኛ ትዕዛዝ ያሉት ሲሆኑ በለእንጀራን የሚመለከቱ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በአዎንታዊና በአሉታ ከመነገራቸው አንጻር በሁለት ይከፈላሉ ይኸውም፡-
1. ሕግ በአሉታ የተነገሩ /አታድርግ/
2. ትዕዛዝ በአዎንታ የተነገሩ /አድርግ/
ከዚህም ሌላ ከአፈጻጸማቸው አንጻር ሲታዩ በሦስት ይከፈላሉ፡፡
1. በሐልዮ የሚፈጸሙ 1፣3፣4 እና 9 በሐሳብ
2. በነቢብ የሚፈጸሙ 2፣ 8 በመናገር
3. በገቢር የሚፈጸሙ 5፣6፣7 እና 10 በሥራ ናቸው፡፡